መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ሮቢ ጋርመንት

ሮቢ ጋርመንት

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ሮቤል ነጋሽ በ2008 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ በዋናነት የሚሠራው የወንዶች ሙሉ ልብስ ሲሆን በዚህም ሥራ በጣም የዳበረ እና የረዥም ጊዜ ልምድ አለው። ከዚህ በተጨማሪ አጠቃላይ አልባሳትን ያመርታል።

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

አቶ ሮቤል ወደ ልብስ ስፌት ሙያ የገቡት ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ የደረሳቸው ትምህርት ጋርመንት በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ አስረድተዋል። ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ ቀጥታ ጥሩ አፕረንቲስሺፕ ከወሰዱ በኋላ አፕረንቲስሺፕ ሲጨርሱ እዛው ድርጅት ቀጥታ ወደ ሥራ ገቡ። በሂደት ሥራውን እየወደዱት መጡ። በጊዜውም ብዙ ሥራ እና ገንዘብ ዐብሮ ስለነበረ የሥራው ፍላጎት በውስጣቸው እያደገ መጣ። በዚህ ሥራ ቀጥለው ለስምንት ዓመት ከሠሩ በኋላ በቂ የሥራ ልምድ ሲአይካብቱ በኋላ የራሳቸውን ድርጅት መሥርተዋል።

ድርጅቱ በዋናነት የሚያመርታቸው ምርቶች ሙሉ ልብሶች ለሠርግ፣ ለምርቃት እና ለሥራ የሚሆኑ ሙሉ ልብሶችን ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ የሕጻናት አልባሳትንም ጨምሮ ይሠራል። ሮቢ ጋርመንት አሁን ባለው የማምረት አቅም በወር 100 (አንድ መቶ) ሙሉ ልብሶችን ማምረት ይችላል።

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች ዋጋ በከፊሉ

  • የህጻናት አልባሳት የብዛት ዋጋ 250 ብር (ሁለት መቶ ሃምሳ ብር) ጀምሮ እስከ 450 ብር (አራት መቶ ብር) ድረስ።
  • ብዛት የህጻናት አልባሳት ለሚወስድ የብዛት ዋጋ 200 ብር (ሁለት መቶ ብር) ነው።
  • የሱፍ አልባሳት ሶስት ፒስ የሚባለው ማለትም ኮት፣ ሱሪ እና ሰደሪያ አካቶ 3,800 ብር (ሦስት ሺህ ስምንት መቶ ብር) ጀምሮ እንደ ሰው ፍላጎት ከፍ ያለ የሚፈልግ ካለ ደግሞ እስከ ብር 4,500 (አራት ሺህ አምስት መቶ ብር) ድረስ ያመርታል።

ድርጅቱ ሲመሠረት በብር 5,000 ሺህ (አምስት ሺህ ብር) ካፒታል ሲሆን አሁን ላይ ብር 500,000 (አምስት መቶ ሺህ ብር) በላይ ካፒታል መድረስ ችሏል። ድርጅቱ በኮሌጆች በኩል በሚመጡ ሥራዎች ከዓመት እስከ ዓመት ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛል። በዚህም ለዐሥር ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል።

ይህ ድርጅት ምርቱን ከሥራው ቦታ ከሚገኙ ተቋማት ከማቅረብ በተጨማሪ በባዛር እና በሄሎ ማርኬት በመጠቀም እያስተዋወቀ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። ጨረታ ላይም በደንብ እየተሳተፈ አይደለም እንጂ ተሳትፎ ሁለት ጨረታዎችን አሸንፎ በሚገባ ሥራውን አከናውኖ ማስረከብ ችሏል። አሁን ደግሞ በከፍታ በነበረው የሥልጠና ስብሰባ ላይ ስለ ከፍታ ያለው ዕውቀት ስለሰፋ ከፍታ ላይ የሚገኙትን አገልግሎቶች በደንብ ለመጠቀም ወስኗል።

የኮቪድ ተፅዕኖ

ኮቪድ ድርጅቱ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ነበረው፤ ሥራም በጣም ቀንሶ ነበር። ሱቆችንም እስከመዝጋት ድረስ ደርሶ ነበር። ይሁን እና ይህን ችግር ለመቅረፍ የድርጅቱ መሥራቾች አዳዲስ ዕይታዎችን መመልከት እንዲጀምሩ አድርጓቸዋል። በዚህም ለብዙ ዓመታት ሙሉ ልብስ ብቻ ሲያመርት የነበረ ድርጅት በጊዜው (በኮሮና ወቅት) የፊት መሸፈኛ ማስኮችን በማምረት ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን ችሏል። በመቀጠል ደግሞ የህጻናት አልብሳት እና ሌሎች የሚሠፉ ነገሮችን በሙሉ በመሥራት ለወደፊት የድርጅቱን አቅጣጫ ወደ ተሻለ መንገድ እንዲሄድ በር በመክፈት ነበር የኮቪድን ጊዜ ያለፈው። ከኮቪድም በኋላ የሕጻናት ልብስ ሥራ ጥሩ ገቢ የሚያስገኝ ሆኖ ስላገኙት ይህን ሥራ በባህላዊ እና ዘመናዊ መልኩ ከልብሶች ጋር አጣምረው መሥራት ቀጥለዋል።

ድርጅቱ በብዛት ምርቱን

  • ኢትዮ ቻይና ኮሌጅ ለሚገኙ ሠራተኞች እና
  • ለሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች ያቀርባል።

አቶ ሮቤል ከኮቪድ የተማሩት ትልቁ ነገር በሚፈጠሩ ወቅታዊ ችግሮች ተስፋ ሳይቆርጡ ያለውን አማራጭ በመጠቀም አዳዲስ ፈጠራዎችን በማምረት ሥራዎችን መሥራት እንደሚቻል ነው። ለምሳሌ አዲስ ዓመት እና ኢሬቻ በዓላት ሲመጡ ምን እንሥራ በማለት ያልተደገሙ ከጊዜው ጋር ሊሄዱ የሚችሉ ሥራዎችን በመሥራት ሥራቸውን ይበልጥ ማሳደግ ችለዋል። በዚህም በደንብ ማደግ እንደሚቻል አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።

ምክር እና እቅድ

አዲስ ወደ ልብስ ስፌት ሙያ የሚገቡ ሰዎች አንደኛ ከምንም በላይ ሙያውን በሚገባ ማወቅ ግዴታ ነው፤ ሁለተኛ ደግሞ ልምድ ማዳበር (በሥራው ላይ በደንብ መሥራት) አስፈላጊ ነው። በተጨማሪ ምን አዲስ ነገር መጣ? ምን እየተሠራ ነው? እንዴት አድርጌ የተሻለ አድርጌ ልሠራው እችላለሁ? የሚሉትን ጥያቄዎችን ሁሌም መጠየቅ እና መመለስ የሚችሉ መሆን አለባቸው ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።

ወደ ፊት ድርጅቱ ገበያ ውስጥ ያለውን የምርት ዕጥረት ለመቅረፍ ምርት በስፋት ይዞ ወደ ገበያ በመግባት ያለውን የገበያ ችግር ብዙ ምርቶችን በማምረት ለመቅረፍ አቅዷል። ይህንንም ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶችን በማምረት እና ለገበያ በማቅረብ በጥራታቸው ስለሚተማመኑ ደንበኛው ራሱ እንዲመጣ እና ብሎም አዳዲስ ደንበኞችን እንዲያመጣ ያደርገዋል። ስለዚህ በዚህም በሰፊው ገበያውን ለመድረስ እና ሥራውን ለማስፋፋት እቅድ አለው።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …